ስለ አርቲስት ፀጋዬ እሸቱ

Tsegaye Eshetu

አርቲስት ፀጋዬ እሸቱ

አርቲስት ፀጋዬ እሸቱ አበበ የተወለደው በ1954ዓ.ም ሲሆን ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ (የተወለደው ጥይት ቤት ያደገው መስከረም ማዞሪያ (ሪቼ) አካባቢ ሲሆን ከ1965 ጀምሮ የካ ነው የሚኖረው) ነው

የፀጋዬ የትዳር አጋር አርቲስት ዘነበች ጌታሁን ዳንሰኛ እና የዳንሰ አሰልጣኝ ስትሆን ግማሽ ሳይሆን ሙሉ አካሌ ነች እያለ ነው የሚገልጻት፡፡ ፀጋዬ የልቤ ፀጋዬ እና ባምላክ ፀጋዬ የሚባሉ ሁለት ልጆች አባት ነው

ፀጋዬ ሙዚቃ የጀመረው በ1969 አካባቢ ሲሆን የከፍተኛ 16 ኪነት ቡድን አባል ነበር ፤ ቀጥሎም በ1976 ከሕንጻ ኮንስትራክሽን ባንድ ጋር መስራት ጀመረ፡፡ የመጀመሪያ የመተዋወቂያ ዘፈኑ አይኖሩም የማያነቡ አይኖች ፤ አይኖሩም የማይጽፉ እጆች የሚለው ስራ ነበር

ፀጋዬ የልጅነት ህልሙ ሙዚቃ ሳይሆን እግር ኳስ ነበር ነገር ግን አሁን ላይ ሆኖ ሲያስበው በሙዚቃ ሕይወቱ የደረሰበት ደረጃ ትልቅ ስኬት ያገኘበት ብቻ ሳይሆን የሚወደው ሞያ በመሆኑ ከኳስ ወደ ሙዚቃ መቀየሩ በቁጭት ሳይሆን በበጎ ነው የሚያየው

ፀጋዬ የመጀመሪያ አልበሙን ለማውጣት ነገሮች ቀላል አልሆኑለትም ቢያንስ ከአራት ዓመታት በላይ ብዙ ሙዚቃ ቤት መመላለሱን እንደውም አልበም ለማውጣት ጊዜ ከመውሰዱ የተነሳ እጁ ላይ የነበሩት የደረጄ ተፈራ ዜማ የሆኑት እየቆረቆረኝ እና መውደድ ነይ ነይ የሚሉ ዘፈኖች በወቅቱ የአርቲስት ቴዌድሮስ ታደሰ አልበም በመቅደሙ እሱ እንዲዘፍናቸው መደረጉን ያስታውሳል

ፀጋዬ በብዙዎች ሕይወት ውስጥ የራሱ ቦታ ያለው የተወደዱ አልበሞች ያበረከተልን ዝነኛ አርቲስት ነው፡፡ ፀጋዬ ለብቻው ከሰራቸው አዳዲስ አልበሞች በተጨማሪም የቀደሙ ስራዎቹን የያዘ ኮሌክሽን አሳትሟል ከዚህም ባሻገር ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመሆን በጋራ የሰራቸው ብዙ ስራዎች ለሕዝብ አድርሷል

ፀጋዬ እሸቱ ሲነሳ በብዙ ሰው አዕምሮ ውስጥ የሚታወሱ እጅግ ተወዳጅነት ያተረፉ ፣ የማይሰለቹ እና ከትውልድ ትውልድ እንደ አዲስ የሚሰሙ ዘፈኖቹ ብዙ ናቸው ተከለከለ አሉ ፣ የአይኔ አበባ ፣ ያየ አለ ፣ ወርቀዘቦ ፣ እስቲ አልምዱኝ ፣ እሄዳለሁ ድሬ ፣ ያ ዘመን ፣ ሙና ፣ ዘምናኒት ፣ ሰንደቅ አላማ ፣ ለሰርጓዋ ተጠራሁ ፣ ገልግለኝ ፣ ፍቅርን ስሪበት ፣ ተጓዥ ባይኔ ላይ እና ሌሎችም ልብን የሚሰርቁ አእምሮን በትዝታ ይዘው ጭልጥ የሚሉ እና ምርጥ ዘፈኖች ተጠቃሽ ናቸው

የፀጋዬ አድናቂዎች ሲገልጹት ብዙ ዘፈኖቹ ስትሰማቸው ያለፈውን ዘመን ትዝታ በዓይነ ሕሊናህ የሚያሳይ ርብሽብሽ የሚያደርግ እና የራስህን ሕይወት የሚነግርህ ያህል የሚሰማህ ምርጥ ስራዎች ያበረከተልን ታላቅ አርቲስት ነው ይላሉ፡፡ የፀጋዬ ስራዎች ከትልቅ እስከ ትንሽ ያለ እድሜ ልዩነት የሚሰማቸው እና አብሮ የሚዘፍናቸው ናቸው

ፀጋዬ ተግባቢ ፣ ቀለል ያለ ሕይወት የሚኖር እና ለሌሎች ህይወት በጎ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስራ መስራት የሚወድ ሰው ነው፡፡ ፀጋዬ እሸቱ በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ይካፈላል ፤ ለተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ህይወት መሳካት የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል

ጸጋዬ በሞያው እና ባለው ተቀባይነት ከሌሎች የሞያ አጋሮቹ ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎች ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ እና የተቻለውን ሁሉ በቁርጠኝነት ለማበርከት ወደ ኋላ የማይል ሙዚቀኛ ነው ፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ የቅጂ መብት በተመለለከተ የተለያዩ ማህበራት ተቋቁሞ በነበረበት ወቅት የድምጻዊያን ማህበር አባል እና የማህበሩ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግሏል እያገለገለም ነው

ጸጋዬ ለአሞራው ባንድ መመስረት ምክንያት የነበረ እና በ1979 የተመሠረተው አክሱማይት ባንድ ባለቤት ነው ፀጋዬ በአሁን ሰዓት በተለያዩ መድረኮች ስራዎቹን ለአድናቂዎቹ እያቀረበ ሲሆን ቀጣይ ስራውን በመስራት ላይ ይገኛል

Join Tsegaye Eshetu on Social Media
Scroll to Top